አማርኛ: Open Bible Stories

Updated ? hours ago # views See on DCS

1. ፍጥረት

OBS Image

ከዚህ ቀጥሎ የምንመለከተው እግዚአብሔር የሁሉም ነገር ጀማሪ መሆኑን ነው። ስለሆነም እግዚአብሔር ዓለምንና በውስጧ የሚገኙትን ነገሮች በስድስት ቀናት ፈጠረ። እግዚአብሔር ምድርን ከፈጠረ በኋላ ምድር ጨለማና ባዶ ነበረች፤ በውስጧምንም ነገር ገና አልተፈጠረም ነበር። ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር መንፈስ በውሆች ላይሰፍፎ ነበር።

OBS Image

ከዚያም እግዚአብሔር “ብርሃን ይሁን” አለ ብርሃንም ሆነ። እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደሆነ አይቶ “ቀን” ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም ቀኑን ከጨለማ ለይቶ ጨለማውን ሌሊት ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም በመጀመሪያው ቀን ብርሃንን ፈጠረ።

OBS Image

በሁለተኛው ቀን እግዚአብሔር ከምድር በላይ ያለውን ጠፈር ፈጠረ። ስለሆነም እግዚአብሔር ውሃን ከጠፈር ለየ።

OBS Image

በሦስተኛው ቀን እግዚአብሔር ውሃውን ከደረቁ መሬት እንዲለይ አደረገ። እግዚአብሔርም ደረቁን መሬት “ምድር” ውሃውንም “ባሕር” ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም የፈጠረው ነገር መልካም እንደ ሆነ አየ።

OBS Image

ከዚያም እግዚአብሔር ምድር ሁሉንም ዓይነት ዛፎችንና ተክሎችን ታብቅል አለ፣ እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔርም የፈጠረው ነገር መልካም እንደ ሆነ አየ።

OBS Image

በአራተኛው የፍጥረት ቀን እግዚአብሔር ፀሐይን፣ ጨረቃንና ክዋክብትን ፈጠረ። እግዚአብሔር ቀንና ሌሊትንም ወቅቶችንና ዓመታትንም እንዲለዩ አደረገ። እግዚአብሔርም የፈጠረው ነገር መልካም እንደ ሆነ አየ።

OBS Image

በአምስተኛው ቀን እግዚአብሔር በውሃ ውስጥ የሚኖሩትንና ወፎችን ሁሉ ፈጠረ። እግዚአብሔር ያ መልካም እንደ ሆነ አየ የተፈጠሩትንም ባረካቸው።

OBS Image

በስድስተኛውም ቀን፣ እግዚአብሔር “በምድር ላይ ሁሉም ዓይነት እንስሳት ይሁኑ” አለ። እግዚአብሔር እንዳለውም ሆነ። አንዳንዶቹ የእርሻ ከብቶች፣ አንዳንዶቹ በምድር የሚሳቡ፣ አንዳንዶቹ የዱር እንስሳት ነበሩ። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።

OBS Image

እግዚአብሔር “ሰዎችን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር እነርሱም በምድር ሁሉና በእንስሳት ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ።

OBS Image

ስለዚህ እግዚአብሔር ከምድር አፈር ወስዶ ሰው አድርጐ አበጀና የሕይወትን እስትንፋስ ሰጠው። የዚህም ሰው ስም አዳም ተባለ። እግዚአብሔር አዳም በሚኖርበት ስፍራ አትክልት ተከለና እንዲያለማው እዚያው አስቀመጠው።

OBS Image

በአትክልቱም መካከል እግዚአብሔር ሁለት የተለዩ ዛፎችን ተከለ፤ የሕይወት ዛፍና መልካምና ክፉን መለየት የሚያስችል የእውቀት ዛፎች ነበሩ። እግዚአብሔርም አዳምን በአትክልቱ ስፍራ ካለው መልካምንና ክፉን መለየት ከሚያስችለው የእውቀት ዛፍ በቀር በአትክልቱ ውስጥ ካለው ከየትኛውም ዛፍ መብላት እንደሚችል ተናገረው። ነገር ግን ክፉውንና መልካሙን መለየት ከሚያስችለው ዛፍ ቢበላ እንደሚሞት ተናግሮት ነበር።

OBS Image

እግዚአብሔር ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም እንዳይደለ ተናገረው። ከእንስሳቱ አንዳቸውም የአዳም ረዳት ሊሆኑ አልቻሉም።

OBS Image

እግዚአብሔርም በአዳም ላይ ከባድ እንቅልፍ ጣለበት አንቀላፍቶም ሳለ ከጐድኑ አንዲት አጥንት ወስዶ ሴት አድርጎ ሠራትና ወደ አዳም አመጣት።

OBS Image

አዳምም ባያት ጊዜ እንዲህ አለ፤ “ይህች እኔኑ ትመስላለች ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር አንድ ይሆናል።

OBS Image

እግዚአብሔር ወንድና ሴትን በራሱ መልክ ፈጠረ። እግዚአብሔርም ባረካቸው፤ አላቸውም “ብዙ ልጆችና የልጅ ልጆችም ይኑሩአችሁ ምድርንም ሙሉአት” እግዚአብሔርም የሠራው ነገር በጣም ጥሩ እንደ ነበር አየ። በሁሉም ነገር ተደሰተ ይህ ሁሉ በስድስት ቀን ሆነ።

OBS Image

በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር የመፍጠር ሥራውን ፈጸመ። ስለዚህ እግዚአብሔር ሲሠራው ከነበረው ሥራ ሁሉ አረፈ፤ ሰባተኛውንም ቀን ባረከው ቀደሰውም። ምክንያቱም በዚህ ቀን ከሥራው ሁሉ አርፏልና። እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በውስጧም የሚገኙትን በፈጠረ ጊዜ የተከናወኑት በዚህ ሁኔታ ነበር።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘፍጥረት 1-2።