አማርኛ: Open Bible Stories

Updated ? hours ago # views See on DCS

40. ኢየሱስ ተሰቀለ

OBS Image

ወታደሮቹ በኢየሱስ ላይ ከዘበቱ በኋላ፣ ሊሰቅሉት ወሰዱት። የሚሞትበትን እንዲሸከም አደረጉት።

OBS Image

ወታደሮቹ ኢየሱስን “የራስ ቅል” ተብሎ ወደሚጠራ ስፍራ አመጡትና እጆቹንና እግሮቹን በመስቀል ላይ ጠረቁአቸው። ኢየሱስ ግን፣ “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን ዐያውቁምና ይቅር በላቸው” አለ። ጲላጦስ፣ በምልክት ላይ፣ “የአይሁድ ንጉሥ” ብለው እንዲጽፉና ከኢየሱስ ራስ በላይ በመስቀሉ ላይ እንዲያኖሩት አዘዘ።

OBS Image

ወታደሮቹ በኢየሱስ ልብስ ላይ ዕጣ ተጣጣሉ። ይህንን ባደረጉበት ጊዜ፣ “ልብሶቼን ተከፋፈሉ፣ በልብሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” የሚለውን ትንቢት ፈጸሙ።

OBS Image

ኢየሱስ በሁለት ወንበዴዎች መካከል ተሰቀለ። አንደኛው በኢየሱስ ላይ ዘበተበት፣ ሌላኛው ግን፣ “አንተ እግዚአብሔርን አትፈራም? እኛ በደለኞች ነን፣ ይህ ሰው ግን በደል የለበትም” አለ። ከዚያም ኢየሰስን፣ “እባክህን በመንግሥትህ ዐስበኝ” አለው። ኢየሱስ፣ “ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ” ብሎ መለሰለት።

OBS Image

የአይሁድ መሪዎችና በሕዝቡ መካከል የነበሩ ሌሎች ሰዎች በኢየሱስ ላይ ተዘባበቱበት። “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ ከመስቀል ላይ ውረድና ራስህን አድን! ከዚያ በኋላ እናምንብሃለን” አሉት።

OBS Image

በዚያን ጊዜ እኩለ ቀን ቢሆንም፣ በአካባቢው ሁሉ ላይ ሰማዩ ፍጹም ጨለማ ሆነ። ከእኩለ ቀን እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ እንደ ጨለመ ቆየ።

OBS Image

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ፣ “ተፈጸመ! አባት ሆይ፣ ነፍሴን በእጅህ እሰጣለሁ” ብሎ ጮኸ። ከዚያም ራሱን አዘነበለና መንፈሱን ሰጠ። በሞተ ጊዜ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፣ በቤተ መቅደስ የነበረው ሕዝቡን ከእግዚአብሔር መገኘት የለየው ትልቁ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ።

OBS Image

ኢየሱስ በሞቱ በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲመጡ ለሰዎች መንገድ ከፈተላቸው። ኢየሱስን ይጠብቅ የነበረው ወታደር የሆነውን ሁሉ ባየ ጊዜ፣ “በእርግጥ ይህ ሰው በደል የለበትም። የእግዚአብሔር ልጅ ነው” አለ።

OBS Image

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ያመኑ ሁለት የአይሁድ መሪዎች፣ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ የኢየሱስን ሥጋ እንዲሰጣቸው ጲላጦስን ለመኑት። ሥጋውን በጨርቅ ገነዙትና ከአለት በተወቀረ መቃብር አኖሩት። ከዚያም ክፍቱን ስፍራ ለመዝጋት ከመቃብሩ ፊት ለፊት ትልቅ ድንጋይ አንከባለሉ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 27፡27-61፤ ማርቆስ 15፡16-47፤ ሉቃስ 23፡26-56፤ ዮሐንስ 19፡17-42።